የጣፊያ ካንሰር፤ መንስኤ፣ ምልክቶችና ህክምና…

የጣፊያ ካንሰር፤ መንስኤ፣ ምልክቶችና ህክምና…

የጣፊያ ካንሰር ሰዎችን በብዛት ለሞት ከሚዳርጉ የካንሰር ህመም አይነቶችው ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል።

ምክንያቱ ደግሞ በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ መታየት አለመቻሉ ነው ይባላል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 በእንግሊዝ ብቻ 9 ሺህ 600 ሰዎች በህመሙ መያዛቸው በህክምና የታወቀ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ ከ8 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

የጣፊያ ካንሰር ስሙ እንደሚያመለክተው ከሰውነታችን ክፍል አንዱ የሆነውን ጣፊያችንን የሚያጠቃ የበሽታ አይነት ነው።

የጣፊያ ስራ ኢንዛይሞችን ማምረት ሲሆን፥ ኢንዛይሞቹም ምግብ ለመፍጨት እና በደማችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር የሚረዱ ናቸው ተብሏል።

የጣፊያ ካንሰር ምልክቶች

በብዛት ከሚስተዋሉ የጣፊያ ካንሰር ምልክቶች ውስጥ አንዱ የላይኛው የሆዳችን ክፍል አካባቢ የሚስተዋል ህመም ሲሆን፥ ህመሙ አንዳንዴ ወደ ጀርባችን ዞሮም ሊሰማን ይችላል።

የህመሙ ስሜት መጀመሪያ ላይ ይከሰትና ወዲያው እንደሚጠፋ የተነገረ ሲሆን፥ ምግብ ከተመገብን በኋላ በምንተኛበት ጊዜ ግን ከፍተኛ የሆነ የህመም ስሜት ይሰማናል ነው የተባለው።

ሌላው ምልክት ደግሞ ድንገተኛ የሆነ የሰውነት ውፍረት (መጠን) መቀነስ፣ የሰውነት ቆዳ ቀለም ወደ ቢጫነት መቀየር ሲሆን፥ የሰገራ ቀለም መለዋወጥ እና የሽንት ቀለም ወደ ደማቅ ቢጫነት አሊያም ብርቱካናማነት መቀየርም የህመሙ ምልክት ሊሆን ይችላል። 

ከዚህ በተጨማሪም፦

  • ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ
  • ከፍተኛ የሰውነት ትኩሳት እና ማንቀጥቀጥ
  •  ምግብ አለመፈጨት
  • የደም መርጋት
  • ከመጠን ያለፍ የሰውነት መዛል ወይም ድካም

እንዲህ አይነት ምልክቶች በብዛት የሚስተዋልብን ከሆነ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ማእከላት በመሄድ የጤና ባለሙያዎችን ማማከር እንዳለብን ነው የሚመከረው።

የጣፊያ ካንሰር ምንስኤ

ምንም እንኳ የጣፊያ ካንሰር ይህ ነው ተብሎ ግልፅ ሆኖ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም፤ የህመሙን ተጋላጭነት የሚጨምሩ ምክንያቶች ግን ይታወቃሉ።

ከእነዚህም ውስጥ እድሜ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ውፍረት (ክብደት) እና የመሳሰሉት የጣፊያ ካንሰር ተጋላጭነትን እንደሚያሰፉ ነው የሚነገረው።

የጣፊያ ካንሰር ህክምና 

የጣፊያ ካንሰር ህክምና በህመሙ አይነት እና ከካንሰሩ የሚገኝበት ስፍራ እንዲሁም የሚገኝበት ደረጃ ላይ ተመስርቶ እንደሚለያይ ነው የጤና ባለሙያዎች የሚያብራሩት።

ዋናው ኢላማ የካንሰር እጢውን ከሌሎች የካንሰር ህዋስ ጋር ሙሉ በሙሉ ጠርጎ ማስወጣት ሲሆን፥ ይህ ካልሆነ ግን የካንሰር እጢው እንዳያድግ የሚከላከል ህክምና ይሰጣል። 

የጣፊያ ካንሰርን ለማከም ሶስት አይነት ይህክምና መንገዶች እንዳሉ የሚያብራሩት የህክምና ባለሙያዎቹ፥ የመጀመሪያው ህክምና በቀዶ ጥገና የካንሰር እጢውን ሙሉ በሙሉ ማስወደግ ነው ይላሉ።

ሌሎቹ የህክምና መንገዶች ደግሞ የካንሰሩ መጠን እንዳይሰፋ የሚያደርግ እና የህመም ስሜቱ እንዲቀንስ የሚረዱ የኬሞቴራፒ እና ራዲዮቴራፒ ህክምናዎች መሆናቸውንም ያብራራሉ።

ምንጭ፦ ሁፊንግቶን ፖስት