የረፈደ ስዓት

የረፈደ ስዓት
የረፈደ ስዓት
(ደራሲ፡-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ)
የፍቅረኛዋን የሚፍጅ ትንፋሽ መሞቅ አምሯት ነበር በምሽት ወደ ቤቱ የመጣችው፡፡እሱ ግን ካለ ልማዱ አምሽቷል፡፡ተንቀሳቃሽ ስልኩም ጥሪ አይቀበልም፡፡ቁልፍ ስለነበራት ከፍታ ወደ ውስጥ ዘለቀች ፡፡ ልትጠብቀው፡፡
ዬሴፍ እና ዳናዊት ከተዋወቁ ገና ሁለት ወራቸው ነው፡፡እሱ ከልቡ አፍቅሯት እሷ ደግሞ ወንዶች ላይ ባላት ጥላቻ ልትበቀለው ነበር የተቀራረቡት
ከቀናቶች ግንኙነት ቡኃላ ግን የእሷ ጠጣር ልብ መደርመስ እና መፈራረስ ጀመረ፡፡ ርህራሄው…እርጋታው …አሳቢነቱ ትንፋሾ ቁርጥ እስኪል እንድታፈቅረው አስገደዳት፡፡እናም የእውነቷን አፈቀረችው፡፡ማፍቀሯ ደግሞ ፀፀት ላይ ጣላት፡፡ቢሆንም በእፍረቶ ውስጥ ተሸሽጋ ቢሆንም በእየዕለቱ እድገት የሚያሳየው ግንኙነታቸው ቀጥሎል።
አሁን በዚህን ሠዓት ሣታስበው ዓይኔቾ አረፍ ለማለት በተጋደመችበት አልጋ ጎን ካለ ኮመዲኖ ላይ በተቀመጠ የዬሴፍን ዲያሪ ላይ አረፉ። የማንበብ ረሀብ አንጀቷን ቦረቦራባት፡፡ስለ እሱ ማንነት ይበልጥ ለማወቅ ፈለገች የመጀመሪያውን ገጽ ስትገልጽ ክፍል ሁለት ይላል፡፡አንድ ሙሉ ሌላ ዲያሪ አለው ማለት ነው ስትል አሰበች፡፡ገለጠች፡፡ሁለተኛ ገጽ
ጥር30/2001 ዓ.ም
ከመኝታዬ የተነሳውት በጥሩ ስሜት ነው፡፡ከህይወት ጋር ፍቅር ይዞኛል፡፡በቃ ተፈጥሮ እንዳለ ያጎጎል፡፡የፀሀዬ ሙቀት…የዛፎቹ አረንጎዴነት…የወፎቹ የሚመስጥ ዝማሬ…የሰዎች ከወዲህ ወዲይ መርመስመስ ይሄን ሁሉ በፍቅር ስታዘብ ነው የዋልኩት፡፤ሁሉም ነገር እጅግ ማራኪ ነው፡፡ምሽት ላይ ለአንድ ሰዓት ገደማ ከዳናዊት ጋር ኦኖምፒክ ካፌ ነበርኩ፡፡ ደስ የሚል ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም በቆይታችን እሷም የተደሰተች ይመስለኛል፡፡በእውነት ዳናዊትን በጣም አፈቅራታለው፡፡ጣፋጭ ልጅ ነች፡፡
እንደሚያፈቅራት ቀድሞውንም ብታውቅም ያነበበችው ንባብ ከእነ ጥልቀቱ እና ግዝፈቱ አረጋገጠላት፡፡ሶስተኛውን ገጽ ገለበጠች፡፡ማንበቦንም ቀጠለች
የካቲት5/2001 ዓ.ም
ከቀኑ 5፡00 ሰዓት
የትም መሄድ አላሰኘኝም፡፡ተበሳጭቼያለው፡፤ምን አልባት ዳናዊት ስለናፈቀችኝ ይሆናል፡፡በዚህ ሰዓት እንደማላገኛት አውቃለው፡፡የዕድሜ ማራዘሚያ መድሀኒቷን ለመውሰድ ሆስፒታል ትሄዳለች፡፡
ተስፈንጥራ ከአልጋው ላይ ተነሳች፡፡ቆመች፡፡ተመልሳ ተቀመጠች፡፡እንዴት ሊያውቅ ቻለ፤›መላሽ አልነበረም የበሽታው ተጠቂ እንደሆንኩ እያወቀ ነው እንዴ ያፈቀረኝ፡፡ነገሮች ሁሉ ተመሰቃቀሉባት እያወቀ አፈቀረኝ ማለት እሱም እንደኔው በበሽታው ተይዞል ማለት ነው፡፡የማወቅ ጉጉቶ ናረ፡፡አራተኛውን ገጽ ገለበጠች
የካቲት20/2001 ዓ.ም
ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት
በዳናዊት ላይ የማስተውለው የመረበሽ ስሜት እኔንም እየረበሸኝ ነው፡፡ምን እንደሚያንገበግባት ብገምትም ልጠይቃት ግን ድፍረት አላገኛውም፡፡ስሜቷን ምጎዳው እየመሰለኝ ተሳቀኩ፡፡በመጀመሪያ የፍቅር ጥያቄ ሳቀርብላት ሳታፈቅረኝ እሺ እንደለችኝ አውቃለው፡፡ቡኃላ ግን ትክክለኛ ዓላማዋን ደረስኩበት፡፡የበቀል ጥማቷን ለመርካት እኔን እንዳጨችኝ ትረዳው፡፤የተሳሳተ ሀሳቧን በሂደት ላስቀይራት እና ወደ ትክክለኛው የፍቅር መንደር ልመልሳት እንደምችል ተስፍ አድርጌ ስለነበር በወቅቱ ብዙም ቅር አላለኝም፡፡
እርግጥ እኔ ከ.ኤች.አይ.ቪ ነፃ መሆኔን ሁለት ጊዜ ተመርምሬ አረጋግጨየያለው፡፡ቢሆንም በእኔ ህይወት ላይ ምንም የሚያመጣው ለውጥ ስለሌለ እያወቅኩ አፍቅሬያታለው፡፡ ዛሬ ግን ምን አልባትም ይዞኝ ሊሆን ይችላል… ነፃም ልሆን እችላለው፡፡ያ ግን እኔን አያስጨንቀኝም በአሁኑ ጊዜ ዳናዊትን በፀፀት እያሰቃያት ያለው ይሄ ጉዳይ ያይመስለኛል፡፡ምንም የገባት ነገር የለም፡፡ሚስጥሯን በምን አይነት ተአምር ሊደርስበት እንደቻለ ግንዛቤው የላትም፡፡ ለዛውም እሱ ነፃ ሁኖ ሳለ እያወቀ ከእሷ ጋር ጥንቃቄ ያልታከለበት ግንኙነት ለማድረግ ለምን እንደወሰነ መልስ የሌው ጥያቄ ሆኖባታል፡፡መልስ ባገኝ ብላ ቀጣዩን ገፅ ገለበጠች፡፡ንባቧንም ቀጠለች፡፡
መጋቢት10/2001
ከምሽቱ 4፡20 ሰዓት
ቀኖቹ እንዴት ተስፈንጥረው እንደሚያልፉ ግራ እየገባኝ ነው፡፡ ሳይረፍድብኝ መፍጠን እንዳለብኝ ስለገባኝ ዛሬ ከጠበቃዬ ጋር ንብረቶቼን ቦታ ቦታ ሳሲዝ ነው የዋልኩት፡፡በዕድሜዬ የሰበሰብኮቸውን ቁሳቁሶች ለምወዳቸው ሁለት ሰዎች በህጋዊ መልኩ አስተላልፌላቸዋለው፡፡ጠቅላላ የንብረቴ ተመን ወደ ሰባት መቶ ሺ ብር የሚጠጋ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ሶስት መቶ ሺ ብር ለዳናዊት ቀሪውን አራት መቶ ሺብሩን ደግሞ ለእናቴ፡፡በእውነት ባደረግኩት ነገር ደስታ ተሰምቶኛን እሩጫዬን ልጨርስ እርምጃ ብቻ ነው የቀረኝ፡፤ዛሬ ጥሩ እንቅልፍ የምተኛ ይመስለኛል፡፡መጮኸ አማራት፡፡ ህልም እያለምኩ ነው እንዴ የራሷን አዕምሮ ትክክለኝነት ተጠራጠረች…እሷ እንኳን ገና ብዙ እኖራለው ብላ በተረጋጋችበት ወቅት እሱ የምን ኑዛዜ ነው፡፡ነው ወይስ አገር ለቆ ሊጠፋ ነው?፡፡እንደዛ ቢሆን ደግሞ ቢያንስ ባንክ ያለውን ተቀማጭ ጥሬ ገንዘቡን ይዞ ይሄድ ነበር:: እራሱን ሊያጠፋ ይሆን ?እንዴ በፍፁ ም እንዲህ ያለ መንፈሰ ጠንካራ ሰው እራሱን ሊያጠፋ አይችልም::የሁኔታዎች አካሄድ ፍፁም ከግምቷ ውጭ እየሆነብት አስላስቸገራት የሚቀጥለውን ገፅ ምን ጉድ ሹክ እንደሚላት በፍራቻ እና በጉጉት መካከል ተጣብቃ ለማንበብ ገልብጣ ዓይኖቾን ስትወረውር ጆዎቾ የበር መንኮኮት ድምጽ ሰሙ…ተንደርድራ ከመኝታ ክፍሉ በመውጣት የሳሎኑን በር ከፈተች፡፡ለሰላምታ እንኳን ጊዜ አልሰጠችውም፡፡
‹‹ምንድነው ይሄ ጉድ?››
ዲያሪውን አስታቀፈችው፡፡ደነገጠ‹‹ አነበብሺው እንዴ?››
ለማንበብ ሞክሬ ነበር አንዱም ግን አልገባኝም ተረጋጊ…‹‹ ቁጭ በይና እናወራለን››
‹‹ቁጭ አልልም ብቻ እያንዳንዷን ነጠላ ነገር ማወቅ እፈላጋለው››ቀጠለች
‹‹እኔን ለፍቅር ስትጠይቀኝ በ ኤች.አይ.ቪ እንደተያዝኩ ታውቅ ነበር?››
‹‹አዎ››
‹‹መድሀኒቱንም እንደምጠቀም?››
‹‹በትክክል›መለሰላት
‹‹በውቅቱ ነፃ መሆንህን በምርመራ አረጋግጠኽ ነበር?››
‹‹አረጋግጬያለው፡፡››
‹‹እያወቅክ ግን ያለኮንደም ግኑኝነት እንድንፈጽም ስጋብዝህ አደረግከው?››
‹‹እዚህ ላይ ተሳስተሸል ያለኮንደም እንድንገናኝ የጠየቅኩሽ እኔው እራሴ ነኝ››
‹‹አይደለም …አይደለም አትዋሸኝ›
‹‹በናትሽ ተረጋጊ››
‹‹ምንም አልረጋጋም.. እሺ ይሄንን ለጊዜው እንተወዉ ..ለመሆኑ ገና በሰላሳ አመትህ ወደ ኑዛዜ ያስኬደህ ምን አይነት ተአምር ነው?››
‹‹እሱን እንኳን ልነግርሽ አልችልም›በማለት መለሰላት በጭንቀት ዓይን ዓይኖን እያየ
በዚህ ጉዳይ ላይማ በቂ ማብራሪያ እፈልጋለው፡፡ከረሳኽው ላስታውስህ እኔ እና አንተ ከተዋወቅን ገና ሁለት ወራችን ነው፡፡ተሳስመን እንኳን አልተጠጋገብንም፡፡ይህም ሆኖ ሶስት መቶ ሺ ብር አውርሰኸኛል፡፡ታዲያ ይሄንን ጉዳይ ዝም ብዬ በድፍኑ የምቀበልኽ ይመስልኸል?››
‹‹በፈጠረሽ በፍቅራችን ልማፀንሽ.. ቀኑ ሲደርስ ሁሉንም በዝርዝር ትረጂዋለሽ››
‹‹ቀኑ እስኪደርስ አልጠብቅም… አንዲትም ቀን መታገስ አልችልም፡፡ ለመሁኑ ለእናትህስ ነግረሀታል?፡፡ይሄንን ጉድ ታውቃለች?
‹‹ኸረ በፈጠረሽ ምንም የምታውቀው ነገር የለም፡፡››
እንግዲያው በለሊት እነሳና ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሄዶ በፊት ደርሼባት ወድ ልጆ አራት መቶ ሺ ብር እንዳወረሳት የምስራቹን አበስራታለው
ግንባሩ ላይ ላብ ችፍ አለ‹‹ አታደርጊውም …ልብ ድካም በሽታ እንዳለባት የነገርኩሽ መሰለኝ ልትገያት ካላሰብሽ በስተቀር በፍጹም አትነግሪያትም
‹‹እንግዲህ ወንድም አለም ያለህ ሁለት ምርጫ ይመስለኛል የመጀመርያው ምርጫ እያንዳንዶን ነገር በግልፅ ለእኔ ማስረዳት …ይሄ ካልተመቸህ ደግሞ ነገውኑ እዛው ጠበቃህ ጋር ትሄድና እኔን ከውርሱ ሰነድ ላይ ታሰርዘኛለኸ፡፡ከዛ ቡኃላ ግን አይኔን ለማየት እንዳትሞክር፡፡ከእነዚህ ከሁለቱ ምርጫዎች በአንዱ አለመስማማት ግን እኔን ወደ ጭካኔ ይመራኛል ወደ እናትህ ለመሄድ እገደዳለው››
‹‹ኦ አምላክ ምን አይነት አጣብቂኝ ውስጥ ነው የከተትከኝ፡፡ ዳን እኔ እኮ በየቀኑ እየሞትኩ ያለው ሰው ነኝ…. ምን አልባት አንድ ወር ብቻ ይሆናል ይሄንን አየር የምምገው…ያንቺን ውበት የማደንቀው…የእናቴን ሽሮ የምበላው››
‹‹አልገባኝም?››
በሀኪም የመሞቻ ቀኔ ተቆርጦ ተነግሮኛል… ሰውነቴ በነቀርሳ ተበልቶ አልቆል …በቃ የመሰናበቻ የሚሆኑ ጥቂት ቀናቶች ብቻ ናቸው የቀሩኝ፡፡››
ተንደርድራ ተጠመጠመችበት….. ወደ ውስጦ ጨመቀችው….የሆነ የምትደብቅበት ጥጋት የምትፈልግ ትመስላለች፡፡ማልቀስ እንኳን አልቻለችም…መጮኸ …ማንቧረቅ…መነፍረቅ.አሰኝቷት ነበር፡፡ጉሮሮዋን ግን ማላቀቅ ተስናታል ፡፡እግዚያብሄርን ዳግመኛ ተቀየመችው፡፡