የኔዘርላንድ አቃቤ ህጎች በቀይሽብር ወንጀል የተከሰሰው ሰው የእድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድበት ጠይቀዋል፡፡

የኔዘርላንድ አቃቤ ህጎች በቀይሽብር ወንጀል የተከሰሰው ሰው የእድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድበት ጠይቀዋል፡፡

በኔዘርላድ አቃቤ ህጋን ባልተለመደ መልኩ ኢትዩጲያዊው የኔዘርላንድ ዜግነት ባለቤት በኢትዩጲያ በ1970ዎቹ የቀይ ሽብር ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ የተከሰሰው ሰው በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ጉዳዩን ከያዙት አቃቤ ህጎች አንዱ የወንጀሉ ክብደት እንዲሁም የተጠቂዎችን እና ዘመዶቻቸውን ጉዳት ከግምት በማስገባት ለወንጀሉ የእድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድበት እንጠይቃለን ሲል በሀግ በሚገኘው ፍርድ ቤት ተናግሯል፡፡
እሸቱ አለሙ የተባለው የ63 አመት ተከሳሽ በጦርነት ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን በቀይ ሽብር ወቅት አሰቃቂ የሆነ ዘመቻ በማካሄድ፤ የደርግን ተቃዋሚዎች በማሰቃየት እና በመግደል ወንጀል ተከሶ ነው ፍርድ ቤት የቀረበው፡፡

ተከሳሹ በኔዘርላንድ አቃቤ ህጋን በመቶ ገጽ የተጠናቀረ እና አብዛኛዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች የሆኑ 321 ተጠቂዎችን የወንጀሉ ሰለባ በማድረግ የቀረበበትን አራት የክስ መዝገብ ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ምላሽ ሰጥቶበታል፡፡ 
ተከሳሽ አቶ እሸቱ ወንጀል ፈጽሞባቸዋል ከተባሉት 321 ሰዎች እ.ኤ.አ ነሀሴ 1978 ላይ 75ቱን በመግደል በአንድ ቦታ አስከሬናቸው እንዲቀበር አድርጓልም ተብሏል፡፡
ነገር ግን ተከሳሹ የሰዎቹን ግድያ አላዘዝኩም ሲል ለፍርድ ቤቱ ቃሉን በሰጠበት ወቅት ተናግሯል፡፡
አሁን ከ40 አመት በፊት በቀይሽብር ዘመቻ ፈጽሟል ለተባለው ወንጀል በፍርድ ቤት እየተጠየቀ ያለው የ63 አመቱ ሰው ወደ ኔዘርላንድ በ1990ዎቹ የገባ ሲሆን እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1998 የሀገሪቱን ዜግነት አግኝቷል፡፡ በኢትዩጲያ ሞት ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን ይህ ግን በኔዘርላንድ ሊተገበር አልቻለም፡፡
በቀይሽብር ወንጀል የተከሰሰው እሸቱ አለሙ ጉዳይ በቀጣይ ሳምንትም በፍርድ ቤቱ እንዲታይ ቀጠሮ የተሰጠው ሲሆን በህዳር ወር አጋማሽ ላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡/ዛሚ ኤፍኤም/