የዚምባቡዌ ወታደራዊ ሀይል ስልጣን መያዙን እየገለፀ ነው

የዚምባቡዌ ወታደራዊ ሀይል የሀገሪቱን ስልጣን መቆጣጠሩን አስታውቋል።

የሀገሪቱ ጦር ስልጣኑን የተቆጣጠርኩት ወንጀለኞች በፕሬዚዳንት ሙጋቤ ዙሪያ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማስቆም ነው ብሏል።

የዚምባቡዌ ጦር ባወጣው መግለጫ፥ የሀገሪቱን ስልጣን መቆጣጠር ያስፈለገው በፕሬዚዳንት ሙጋቤ ላይ ወንጀል ለመስራት እያሴሩ ያሉ ወንጀለኞችን ለመከላከል መሆኑን አስታውቋል።

የ93 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ እና ቤተሰቦቻቸው ሙሉ በሙሉ ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን የሀገሪቱ ጦር በመግለጫው አረጋግጧል።

የዚምባቡዌ ወታደሮች እና የጦር ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገሪቱ ዋና ዋና የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ፓርላማ እና ፍርድ ቤቶች የሚወስዱ መንገዶችን መዝጋታቸውንም የአይን እማኞች ተናግረዋል።

በርካታ የዚምባቡዌ ዜጎችም ጥሬ ገንዘብ ከባንክ ለማውጣት በባንክ ቤቶች በር ላይ ረጃጅም ሰልፎች ይዘው ታይተዋል።

የዚምባቡዌ ጦር ሜጀር ጀነራል ኤስቢ ሞዮ፥ የጦሩ እያካሄደ ያለው ዘመቻ ዋናኛ ኢላማ በፕሬዚዳንት ሙጋቤ ዙሪያ ያሉ ወንጀለኞች ላይ ነው ብለዋል።

“እነዚህ ወንጀለኞች በሀገሪቱ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲከሰት እያደረጉ ነው” ያሉት ሜጀር ጄነራል ኤስቢ ሞዮ፥ የዚምባቢዌ ጦር የወሰደው እርምጃም እነዚህን ወንጅለኞች ለህግ ለማቅረብ ነው ብለዋል። 

“ዘመቻችንን እንደጨረስን አሁን ያለው ሁኔታ ወደ ቀድሞው እንደሚመለስ እምነት አለኝ” ሲሉም ተናግረዋል።

የዚምባቡዌ ጦር የሀገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትር ኢግናቲየስ ቾምቦን በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተሰምቷል።

በትናንትናው እለት ወደ ሀራሬ የገቡት የዚምባቡዌ ወታደሮች የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነውን ዜድ.ቢ.ሲ መቆጣጠራቸውም ተነግሯል። 

የዚምባቡዌ መከላከያ ሀይል ዋና አዛዥ ጀነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌኛ ቀደም ብለው በሰጡት መግለጫ፥ በአገሪቱ የነፃነት ትግል ውስጥ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሰዎች ከስልጣን መወገዳቸው እንዲቀጥል እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።

አጠገባቸው 90 ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን አስቀምጠው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “በነፃነት ትግሉ የተሳተፉ የዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ አባላትን የማስወገዱ ተግባር መቆም አለበት” ማለታቸው ይታወሳል።።

“ይህን የሚያደርጉ ወገኖች በተግባራቸው ከቀጠሉ ጦሩ ጣልቃ ይገባል” በማለት ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ዋና አዛዥ ጀነራል ኮንስታንቲኖ መግለጫ ተከትሎ ከ24 ሰዓታት በኋላ ነው ጦሩ እርምጃ መውሰድ የጀመረው።/ኤፍ.ቢ.ሲ/