በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚካሄዱ የትምህርትና ሥልጠና ሥራዎች ውጤታማነት ተማሪዎች፣ መምህራን ፣ወላጆችና ህብረተሰቡ ኃላፊነታቸውን በላቀ ደረጃ ሊወጡ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ አስታወቁ፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚካሄዱ የትምህርትና ሥልጠና ሥራዎች ውጤታማነት ተማሪዎች፣ መምህራን ፣ወላጆችና ህብረተሰቡ ኃላፊነታቸውን በላቀ ደረጃ ሊወጡ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ አስታወቁ፡፡


• የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ህብረ-ብሔራዊነትና ኢትዮጵያዊነት የሚገነባባቸው ተቋማት እንጂ ተግባራቸው በጥቂት ችግር ፈጣሪዎች የሚስተጓጎል አለመሆኑንም ገለጹ
• 141ሺህ አዲስ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎች በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በመማር ላይ
መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ክቡር የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ሥራ አጀማመርና መፈጸም ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ተቋማቱ የመማሪያ ፣ የምርምር፣የቴክኖሎጂና የማህበረሰብ አገልግሎት ማዕከላት ናቸው፡፡


ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትምህርትና ስልጠና ባሻገር ህብረ ብሔራዊነትና ኢትዮጵያዊነት የሚገነባባቸው ተቋማት በመሆናቸው መደበኛው የመማር ማስተማር ሥራቸው ሰላምን በማይሹ በጥቂት ተማሪዎች መስተጓጎል እንደሌለበት ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም መንግስት እንደ እናትና አባት ተረክቦ እያስተማረ፣ እየመገበ፣ ህክምና እና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን እያቀረበ የሚያሰለጥናቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ትምህርታቸው እንዳይስተጓጎል ችግር ፈጣሪዎችን ተጠያቂ ሊያደርጓቸው እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
ወላጆችም ልጆቻቸው በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በጥብቅ በመከታተል መምከር እንዳለባቸው፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችና መምህራንም የተቋማቱን ህግና ሥርዓት ማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ክቡር ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ጥያቄ ቢኖራቸው እንኳን አደረጃጀቱን ተጠቅመው በሠላማዊና በህጋዊ መንገድ ሊያቀርቡ እንደሚገባ ጠቁመው ከዚህ ውጪ ሠላምን ለማወክ የሚፈልጉ ችግር ፈጣሪዎች በዩኒቨርሲቲ እንዲቆዩ እንደማይፈቀድላቸው አስታውቀዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቴክኖሎጂ መፍለቂያና የማህበረሰብ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመሆናቸው የየአካባቢው ማህበረሰብም በባለቤትነት ችግር የሚፈጥሩ ውስን ተማሪዎችን አጋልጦ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
በተያያዘ ግብዓት እየተሟላላቸው ያሉት አስራ አንዱ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች በቅርቡ የተመደቡላቸውን ተማሪዎች ለመቀበል የመጨረሻ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ዶክተር ጥላዬ ጠቁመዋል፡፡


በትምህርት ዘመኑ በአጠቃላይ ከ700ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች በ36 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በትምህርት ላይ እንደሚገኙ ከዚህ ውስጥ 141ሺህ ያህሉ አዲስ ገቢ ተማሪዎች መሆናቸውን፣ 43 በመቶ ያህሉ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ጨምረው መግለጻቸውን የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል፡፡