ከ67 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የመለያ ኮድ ተሰጠ፡፡

ከ67000 በላይ ለሚሆኑ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የመለያ ኮድ ተሰጠ፡፡

ለቅድመ መደበኛ፣ ለመጀመሪያ ደረጃ፣ ለሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም አማራጭ መሰረታዊ ትምህርትን ለሚሰጡ ትምህርት ቤቶች ወጥ የሆነ ባለ 11 ዲጂት መለያ ኮድ ነው የተሰጠው።

ሶፍትዌሩ ድግግሞሽ እንዳይኖርና ወጥ በሆነ መልኩ ጥራቱን ጠብቆ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ስራ አመራር መረጃ አቅርቦት እና ICT ዳይሬክቶሬት እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ስራ አመራር መረጃ አቅርቦት እና ICT ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ሚሊዮን በቀለ፣ የትምህርት ቤት መለያ ኮድ መሰጠቱ ከዚህ በፊት በትምህርት ዙሪያ ይገጥሙ የነበሩ የመረጃ አሰባሰብ ተግዳሮቶችን ይቀርፋል ብለዋል፡፡

አያይዘውም በአንድ አካባቢ የሚገኙ ተመሳሳይ የትምህርት ቤት ስያሜዎችን የመለየት ሥርዓት ለመዘርጋት መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የትምህርት ቤት ኮድ ባለመኖሩ የየትምህርት ቤቶችን መረጃ እርስ በርስ ለማነፃፀር አዳጋች ያደርግ የነበረውን ሁኔታ የዚህ ስርዓት መዘርጋት ሊቀርፍና ራሱን የቻለ ጉልህ ድርሻ ሊወጣ እንደሚችል በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ኤንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስፋው መኮንን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይ የተሰጠውን የትምህርት ቤቶች ኮድ እስከ ታች በማውረድና በትምህርት ቤቶች ደጃፍ ላይ በመለጠፍ መረጃ የሚሰበስቡ አካላት ኮዱን አንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡

 

ትምህርት ሚኒስቴር