በሞጆ ከተማ የንግድ ኤግዚቢሽን እና ባዛር ሊካሄድ ነው፡፡

በሞጆ ከተማ የንግድ ኤግዚቢሽን እና ባዛር ሊካሄድ ነው፡፡

ከተመሰረተች ከ120 አመታት በላይ የሆናት ሞጆ ከተማ ለሀገራችን የንግድና ኢንዱስትሪ በተለይም ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የደረቅ ወደብ አገልግሎት የሚሰጥባት ከተማ ናት፡፡

ሞጆ ከተማ ከ145 በላይ የሚሆኑ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ፋብሪካዎች የሚኖሩባትና በሃገራችንም የመጀመሪያው ግዙፍ ደረቅ የሚገኝባት የሎጀስቲክ ከተማ ለመባል የበቃች ስትሆን ከጅቡቲ አዲስ አበባ ለተዘረጋው የባቡር መስመርም አገልግሎት ከሚሰጥባቸው ከተሞች መካከልም አንዷ ናት፡፡

የሞጆ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የልማት አገናኝ ቢሮ የከተማዋን የገበያ ትስስርን ፤ የኢንቨስትመንት አማራጭ መሆንን ፤ የንግድ ማዕከልነትን እንዲሁም የከተማዋን የልማትና ኢንቨስትመንት ገጽታና እንቅስቃሴን ለማሳወቅና ለማሳየት ያግዘኛል ያለውን የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛር ለማካሄድ ከታህሳስ 15 እስከ 28 / 2010ዓ.ም ቀን መቁረጡን አስታውቋል፡፡

 

 

ለ14 ቀናት በሚቆየው በዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር ከ200 በላይ በሚሆኑ በትራንስፖርት ፤ በሎጀስቲክስ ፤ በትራንዚት ፤ በግብርና ፤ በማዕድን ፤ በትምህርት ፤ በፋይናንስ ፤ በምርምር እና በሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ አገልግሎት ሰጭና አምራች ድርጅቶች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡

ሻጭና ሸማች የሚገናኙበት ተጠቃሚና አገልግሎት ሰጭ ምክክር የሚያደርጉበት ይህ ዝግጂት አዳዲስ የስራ ፈጠራዎችና ምርቶችም  እንደሚካተቱበትና እንደሚተዋወቁበት ተገልጿል፡፡

የሞጆ ኤግዚቢሽና ባዛር ለጎብኝዎችና ተሳታፊዎች መልካም የስራ ትውውቅንና ንግድ ትስስርን እንደሚፈጥር የሚጠበቅ ሲሆን በትራንስፖርት ፤ በሎጀስቲክስና በትራንዚት አገልግሎት ዘርፎች ላይ ባሉ ችግሮችና ተግዳሮቶች ላይ የምክክር መድረክ እንደሚደረግም ህዳር 30/2010 ዓ.ም በሞጆ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቢሮ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል፡፡

ሙሉ ጋዜጣዊ መግለጫውን ነገ ይጠብቁን፡፡